የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የመንግስትን የልማት አቅጣጫዎችን ተከትሎ እየተተገበረ በመሆኑ ቀጣይነቱ አስተማማኝ ነው

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የመንግስትን የልማት አቅጣጫዎችን ተከትሎ እየተተገበረ በመሆኑ ቀጣይነቱ አስተማማኝ ነው

======================================================================

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ10 ክልሎችና በ1 የከተማ አስተዳደር በ494 ወረዳዎች እተተገበረ ይገኛል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ/ቤት የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ዴስክ ኃላፊ አቶ በየነ አዳነ የፕሮግራሙ ዋነኛ አላማ፤ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ጥሪታቸው እንዳይመናመን መጠበቅ እና በማህበረሰብ ደረጃ ጥሪት እንዲፈጥሩ በማድረግ የቤተሰብ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከመንግስት የልማት አቅጣጫዎች ጋር በመናበብ የሚተገበር ነው ያሉት ዴስክ ኃላፊው አረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

1 ሺህ 918 የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ፕሮግራሙ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ስነ-አካላዊ እና ስነ-ህይወታዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት የአፈር መሸርሸርን፣ የመሬት መንሸራተትን እና ጎርፍን እየተከላከለ እንደሆነም አክለዋል፡፡

ፕሮግራሙ የሚተገብራቸው እያንዳንዱ ስራዎች ከመንግስት ተቋማዊ አደረጃጀት እና ተግባራት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የልማት ስራው ቀጣይነቱ አስተማማኝ እንደሆነም ዴስክ ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡

በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ፕሮግራሙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የገለፁት አቶ በየነ መንግስት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በርካታ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ዘላቂ የሆነ የኑሮ ማሻሻያ ተግባራት የተሰሩ ሲሆን የአንድ ጊዜ ጥሪት መፍጠሪያ ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ እየተከናወነም ይገኛል፡፡

ለ860 ሺህ የቤተሰብ ሃላፊዎች የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው በመረጡት የስራ መስክ ተሰማርተው እንዲሰሩ በማድረግ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top