


የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የምግብ ዋስትና ዳይሬክተር ወርቁ ከበደ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በድህነት ላሉ የዕለት ምግባቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ በክልሉ ዘላቂ የልማት ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ ድጋፍ እየተሰሩ ያሉ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ የመስኖ አውታር እና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ግንባታ ስራዎችንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃው፣ የመስኖ አውታር ግንባታው እና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ስራ ጋር ተሳስሮ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡

ፕሮግራሙ በ1997 ዓ.ም በክልሉ መተግበር መጀመሩን አስታውሰው፤ በርካቶች በድህነት የነበሩ ኑሯቸው ተሻሽሎ ከፕሮግራሙ እንደወጡ አቶ ወርቁ ገልፀዋል፡፡
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በአብቾ ቀበሌ በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የተገነባው የመስኖ ግድብ በ2009 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በዚህም 28 ሄ/ር መሬት አትክትና ፍራፍሬ እየለማ ይገኛል፡፡
በመስኖ ግድቡ 112 አባወራና እማወራ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከዚህ ውስጥም 38ቱ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ቀጥተኛ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ወረዳና ቀበሌ ተራቁቶ የነበረ መሬት በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ድጋፍ በህብረተሰብ ተሳትፎ 657 ሄ/ር ተፋሰስ ለምቷል፡፡

በተፋሰሱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተሰራ ሲሆን 222 አባወራና እማወራ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በዚህም ምንጮች ጎልብተዋል፣ የአፈር ለምነት ጨምሯል እንዲሁም ለእርሻ ስራ ምቹ መደላደል ተፈጥሮ ምርታማነት እንደጨመረ የተፋሰሱ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ፡፡
ወጣት መሃመድ አደም በቃሉ ወረዳ በአበቾ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ከዚህ ቀደም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ ችግር ገጥሞት እንደተመለሰ ያስታውሳል፡፡


ወጣቱ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ቀጥተኛ ተጠቃሚ ባይሆንም በዚሁ ወረዳና ቀበሌ ፕሮግራሙ ባስገነባው የመስኖ ግድብና ተፋሰስ ተጠቃሚ ነው፡፡
በመስኖ ግድቡ አትክልትና ፍራፍሬ በዓመት ሶስት ጊዜ እያለማ በወር በአማካኝ እስከ 15 ሺህ ብር እንደሚያገኝም ተናግሯል፡፡
በዚህም 4 ልጆቹን በአግባቡ ማስተዳደርና የቤተሰቡን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደቻለ አስረድቷል፡፡
ዜጎች ከህገ-ወጥ ስደት ተቆጥበው መንግስት በሚያመቻቸው የስራ ዕድል በመጠቀም ኑሯቸውን ማሻሻል እንደሚችሉ ይመክራል፡፡
ወጣት መሃመድ ኑሮው እንዲሻሻል የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እያደረጉ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል፡፡
