ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ርብርብ የተረጅነት አስተሳሰብን ማስወገድ ይገባል!

የአማራ ክልል የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል የመድረኩን ዓላማ ሲገልፁ፤ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን መገምገምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኑሮ ማሻሻያ፣ በማህበረሰብ ስራ፣ ውሃ በማሰባሰብ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በማምረት ገቢ ማስገኘት እና የፕሮግራሙን አሰራር ማዘመን ላይ በበጀት ዓመቱ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ስራ ተጠቃሚዎች ብድርና የአንድ ጊዜ ጥሪት መፍጠሪያ ድጋፍ በማግኘት በመረጡት የስራ መስክ በመሰማራት ሃብት ፈጥረው ራሳቸውን ችለው በርካቶች ከፕሮግራሙ እየወጡ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

ለ2017 በጀት ዓመት 13 ቢሊየን ብር በጀት ተይዞ ከመቼው ጊዜ በተሻለ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ የገለፁት ኮሚሽነር ተስፋው እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 196 ሺህ 133 የቤተሰብ ኃላፊዎች እስከ ቤተሰቦቻቸው ከፕሮግራሙ ለማስመረቅ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አመራሩ፣ ባለሙያውና የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣት እንዳለባቸው ያነሱት ኮሚሽነሩ ተረጂዎች በተፈጠረላቸው ጥሪት በአግባቡ በመጠቀም ከፕሮግራሙ በውጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አያይዘውም ከፕሮግራሙ ተመርቀው የወጡ እንደገና ወደ ድህነት እንዳይመለሱ ከተረጂነት አስተሳሰብ ተላቀው ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ አበክረን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም ኮሚሽነሩ በ2017 በጀት ዓመቱ የታዩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው መቀጠል አንዳለባቸው አቅጣጫ ሰጥተው፤ የተስተዋሉ ክፍተቶች ደግሞ ትምህርት ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top