




በአማራ ክልል ባቲ ወረዳ ጨቆርቲ ቀበሌ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ፕሮግራሙ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ኑሯቸው እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ እታገኘሁ አደመ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በክልሉ አመርቂ ውጤት እያስገኘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም በኑሮ ማሻሻያ፣ በማህበረሰብ ስራ፣ ውሃ በማሰባሰብ ከፍተኛ ዋጋ ባላቸው ምርቶች ገቢ ማስገኘት እና የፕሮግራሙን አሰራር ማዘመን ላይ በበጀት ዓመቱ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡
የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ስራ ተጠቃሚዎች ብድርና የአንድ ጊዜ ጥሪት መፍጠሪያ ድጋፍ በማግኘት በመረጡት የስራ መስክ በመሰማራት በርካቶች ሃብት በመፍጠር ኑሯቸው እየተሻሻለ ከፕሮግራሙ እየወጡ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ፕሮግራሙ በክልሉ በ11 ዞኖች እና በ87 ወረዳዎች እየተተገበረ እንደሚገኝ የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሯ ፕሮግራሙ መንግስት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚያደርገው ጥረት አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በባቲ ወረዳ ጨቆርቲ ቀበሌ የመስኖ አውታር የተገነባ ሲሆን 10 ሚሊየን ብር ወጪም ተደርጎበታል፡፡
የመስኖ አውታሩ በ2016 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ በዚህም የመስኖ አውታር 43 አባወራና እማወራ ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን 55 ሄ/ር መሬት እየለማ ይገኛል፡፡
አርሶ አደር አብዱ አባጋር በዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ እንደነበሩና በፕሮግራሙ ድጋፍ እራሳቸውን በመቻላቸው ከፕሮግራሙ ከአራት ዓመታት በፊት እንደወጡ ያስረዳሉ፡፡
የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት የቤተሰባቸውን የዕለት ጉርስ መሸፈን ይቸግራቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
ከፕሮግራሙ ብድር ወስደው የእርሻ ስራቸውን አስፋፍተው መስራት እንደቻሉና ተግተው በመስራታቸውም በአጭር ጊዜ ብድራቸውን እንደመለሱ ተናግረዋል፡፡
አርሶአደሩ አያይዘውም የፕሮግራሙ ድጋፍ ቤተሰባቸውን በአግባቡ መምራትና የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዳስቻላቸው ይገልፃሉ፡፡
በሚኖሩበት ወረዳ ፕሮግራሙ ባስገነባው የመስኖ አውታር አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ ቤተሰባቸውን በአግባቡ እያስተዳደሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡
የመስኖ አውታሩን በመጠቀም የሚያመርቱትን የግብርና ምርቶች ለገበያ በማቅረብ በአማካኝ በወር እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚያገኙም ተናግረዋል፡፡
አርሶአደሩ ኑሯቸው እንዲሻሻል የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ላበረከቱት አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
