

“የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እና ጉዳት የደረሰባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የአመዝኮ ውይይት ተካሂደ።
በዞኑ 3 ወረዳዎችና 23 ቀበሌዎች የጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸዉን የገለፀው የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስተና ተ/ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቂያ ምላሽ ቡድን የ2017/18 በጀት ዓመት የጎርፍ መከላከልና መጠባበቂያ ዕቅድ አቅርቦ በአመዝኮ ኮሚቴ አባላት ውይይት ተደርጎበታል።
በጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከችግሩ ጋር ተላምደው መኖርን ምርጫ ማድረጋቸው የአደጋውን ተጋላጭነት እንዲጨምር አድርጎታል ያሉት የኮሚቴው አባላት የህዝብ ሞብላይዜሽን መፍጠር ያስፈልጋል፤ምክንያቱም ጎርፍ ትንሽ ቦታ ሰብሮ ከወጣ በኋላ ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ስለሚሆን በእያንዳንዱ ተግባራት ላይ የማህበረሱ ተሳትፎ የታከለበት ክዋኔ መኖር ይገባዋል ብለዋል።
አሁን ላይ የሚስተዋሉትን በከፍተኛ ጎርፍ የመጥለቅለቅ አደገኛ ምልክቶች መነሻ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በመተጋገዝ ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ አካል መሆን ይገባናል ያሉት የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስተና ተ/ጽ/ቤት ኃላፊና የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ በላይ አስራደ ደጋፊ ድርጅቶች በደረሳቸው መረጃ መሰረት ከውጭም ከውስጥም ሀብት በማሰባሰብ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍሎች መደገፍና መለሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ የዞኑ አመዝኮ ኮሚቴ ሚናውን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ፣ ትምህርት መምሪያ ኃላፊና የአመዝኮ አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደስታ አስራቴ በበጋው ወራት የተሰሩት ቅድመ ዝግጅት ስራዎች መልካም የሚባሉ ቢሆኑም ተቋሙ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ የሰራቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ዘላቂ መፍትሔ መሆን አልቻሉም ብለዋል።
ከዚህ ችግር ለመውጣት ማህበረሰቡን የምናገኝበትን ማንኛውንም የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም ተደጋጋሚ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ያሉት አቶ ደስታ ሁሉም ተቋማት እንደ ተቋማቸው ስራ ባህሪያት አቅደው መስራት እንደሚገባቸውና እንደተቋም ማድረግ የሚቻለንን ድጋፍ በማድረግ ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በየዘርፋችን ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።
የጠራና የተደራጀ መረጃ በመሰብሰብ ለሚመለከተው አካል በወቅቱ እውቅና መፍጠር ይገባል፤ የቴክኒክ ኮሚቴው ዛሬ ነገ ሳይል ከስፍራው ድረስ በመሄድ የጠራ፣የተደራጀና የጋራ ዕውቅና የተያዘበት መረጃ አደራጅቶ ለአቢይ ኮሚቴው ማቅረብና ማስገምገም እንደሚገባ የጠቀሱት አቶ ደስታ ማሰብና መስራት የሚገባን ስለተፈጠረው አሁናዊ ችግር ብቻ ሳይሆን ከዚህ ችግር ባሻገር ስለ ተተኪ ዘር፣ከወባ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተላላፊና የማይተላለፉ በሽታዎች፣ በትምህርትና በኢኮኖሚው ዘርፍ ሊደርስ የሚችለውን ስብራት በማሰብ ጭምር ነው ብለዋል።
በመጨረሻም የቴክኒክ ኮሚቴው በየጊዜው እየተገናኘ መገምገም፣ችግሮችን መቀነስ፣ለአቢይ ኮሚቴው ማሳወቅና ዘላቂ መፍትሔ ለሚያፈላልጉ የምርምር ማዕከላት በግብዓትነት መስራት እንደሚገባው አቶ ደስታ አሳስበዋል።
