




የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP Integrated development solution for IDPs project ) ጋር በመተባበር ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በተዘጋጀው ስትራቴጂ (Durable Solution Strategy for IDPs and Returnees Mainstreaming ) ዙሪያ የክልል የዞንና ወረዳ ባለሙያዎች በተገኙበት አውደ ጥናት አካሂዷል።
የክልል እና የዞን ጤና ፣ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ስራና ስልጠና፣ ገንዘብ ቢሮዎች እንዲሁም የወረዳ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ባለሙያዎችና ቡድን መሪዎች የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ናቸው።


ዋና ዓላማው ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በተዘጋጀው ሰነድ (Durable solution strategy mainstreaming) ላይ ስልጠና መስጠትና ሴክተር ተቋማት የስራቸው አንድ አካል አድርገው ስትራቴጂውን እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው።
አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ አማካሪ የሆኑት አቶ አንሙት በለጠ ሲሆኑ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ከክልሉ ውጭና በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ወገኖች እንዳሉ ገልጸው እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ የተዘጋጀ ስትራቴጂ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በመንግስት ብቻ በቂና ውጤታማ ስለማይሆን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የጋራ ምላሽ የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተዘጋጀውን ስትራቴጂ (Durable solution strategy) ሰነድ የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ባለሙያ የሆኑት አቶ ከፍያለው ጎላ አቅርበዋል።

በኮሚሽኑ አስተባባሪነት የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራምን (UNDP) ጨምሮ የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቴክኒካል የባለሙያዎች ቡድን በማዋቀር በስትራቴጂ ሰነድ ዝግጅቱ ላይ እደተሳተፉበት አብራርተዋል።
የዓለም አቀፍ ህጎችን ባከበረ መልኩ የተዘጋጀ ስትራቴጂ በመሆኑ ተቋማት የስራቸው አንድ አካልና መመሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ በአጽንኦት አስረድተዋል።
አቶ ከፍያለው ስትራቴጂ ሰነዱ ሲዘጋጅ ከ500 በላይ ተፈናቃዮች በናሙናነት ተመርጠው በጥናቱ እንደተሳተፉ የገለጹ ሲሆን በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሁኔታ፣ ለተፈናቃዮች የሚያጋጥሙ ፈተናዎች፣ የስትራቴጂው ጠቀሜታ እና ወሰን፣ የስትራቴጂውን ዓላማ፣ የመመሪያ መርሆዎች፣ ነባር ህጎች እና ፖሊሲዎች፣ የዝግጅት ስራዎች እና ዘላቂ የመፍትሄ መንገዶች፣ የቤተሰብ ደረጃ የዳሰሳ ጥናት፣ የሚመራበት መንገድ፣ የሀብት አሰባሰብ እና የክትትል ሁኔታው ምን እንደሚመስልና ተያያዥ ጉዳዮችን በዝርዝር አቅርበዋል።
“ስትራቴጂው መንግስት መር በመሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በዘላቂነት የማቋቋሙን ተግባር በተዘጋጀው መሰረት በባለቤትነት መያዝ እንዳለባቸው አስገንዝበው በሰነዱ የተቀመጡ የመፍትሔ ሀሳቦች ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል ባለሙያው።
መልሶ የማቋቋም ስትራቴጂ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ ለተፈናቃይ የማህበረሰብ ክፍሎች ለማምጣት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ በአውደ ጥናቱ ላይ ተገልጿል። ተፈናቃይና ተመላሽ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት መልሶ የማቋቋሙ ተግባር ከፌደራል መንግስት እስከ ቀበሌ ያሉ አካላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ረጂ ድርጅቶች እና ማህበረሰቡ በቅንጅት (Multi-Sectoral) በሆነ መንገድና በሀላፊነት ሊፈጽሙት እንደሚገባ በስትራቴጂው በግልጽ ተቀምጧል።
ተፈናቃይና ተመላሾችን በዘላቂነት ለማቋቋም በስትራቴጂ ጥናቱ ላይ የተቀመጡ የመፍትሄ ሀሳቦች ወደነበሩበት ቦታ መመለስ፣ አሁን ባሉበት ማህበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ስራዎች እንዲሰማሩና ተረጋግተው እንዲቀመጡ ማድረግ እና ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር የሚሉ ናቸው።
ከሶስቱ አማራጮች እንደ ሀገር ፓለቲካዊ ውሳኔ በመስጠትና ለማቋቋሚያ የሚሆን ሃብት በማፈላለግ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ቀዬ መመለስ በሁሉም ረገድ አዋጭ መፍትሔ መሆኑ ተመላክቷል። ከተመለሱም በሗላ ተረጋግተውና ደህንነት ተሰምቷቸው እንዲቀመጡ፣ የወደሙ ሃብትና ንብረቶቻቸው እንዲመለሱ በማድረግ ዘላቂነት ባለው መልኩ ማቋቋም ተረጅ ሳይሆን አምራች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
በመጨረሻም በቀረበው ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋሚያ ስትራቴጂ ዙሪያ በአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዷል። ለተነሱ ጥያቄዎችና ለተሰጡ አስተያዬቶች በሰነዱ አቅራቢ በአቶ ከፍያለው ጎላ እና ውይይቱን በመሩት የኮሚሽኑ አማካሪ የሆኑት አቶ አንሙት በለጠ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጧል።
ለስትራቴጂው ውጤታማነት የመረጃ አያያዝና ጥራት ወሳኝ እንደሆነና በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስትራቴጂውን የስራቸው አካል በማድረግ ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ማጠቃለያ ተሰጧል።
የስትራቴጂክ ጥናቱ ተፈናቃዮችንና ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም (Durable Solution Strategy for IDPs and Returnees)፣ ዘላቂ በሆነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄዎችን ያሳየ ነው።
