በአማራ ክልል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል በ5 ሺህ 404 ሔክታር ላይ የለማ ሰብል ምርት እየተሰበሰበ ነው

ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል በ2017/18 የመኸር ወቅት በ5 ሺህ 404 ሔክታር የእርሻ መሬት ላይ የለማ ሰብል ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም ለመሸፈን የተያዘውን አጀንዳ ለማሳካት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሠርክአዲስ አታሌ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ሕብረተሰቡ በራሱ ጥረት የምግብ ሉዓላዊነቱን እንዲያረጋግጥና እንዲደጋገፍ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ፤ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም ለመሸፈን ማምረት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር በመኸር ለማልማት ከታቀደው ውስጥ 5 ሺህ 404 ሔክታሩ መልማቱን እና የደረሰው ሰብልም እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህም 216 ሺህ 160 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

በሌላ በኩል በመኸር ወቅት ለማልማት ታቅዶ ያልተከናወነውን በበጋ መስኖ ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

እንዲሁም በተያዘው የበጀት ዓመት ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 1 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ፤ እስካሁን 317 ሚሊየን በር መሰብሰብ መቻሉን አረጋግጠዋል።

በክልሉ መንግሥት ደግሞ ለመጠባበቂያ 200 ሚሊየን ብር መመደቡን ጠቁመው፤ ከተሰበሰበው ጋር እስካሁን 517 ሚሊየን ብር ለሰብዓዊ ድጋፍ እህል ግዥ የሚውል ገንዘብ አለ ብለዋል።

ለምርት ማስቀመጫም በወረዳ፣ በዞንና ከተማ አሥተዳደሮች ደረጃ 181 እንዲሁም በክልል ማዕከላዊ ደረጃ ሦስት ጥራታቸውን የጠበቁ መጋዘኖች መኖራቸውን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም መሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ምክትል ኮሚሽነሯ ያስታወቁት።

ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top