የ2018 ዓ/ም የአካል ጉዳተኞች ቀን “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት – ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡






የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አመራርና ሰራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ፣ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀንን በፓናል ውይይት አክብረዋል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዲ/ን ተስፋው ባታብል አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍ በሁለንተናዊ መንገድ ተጠቃሚ ማድረግና ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል የበዓሉ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
ዲ/ን ተስፋው ባታብል (ኮሚሽነር) እንደ ሀገር፣ እንደ ክልል ብሎም እንደተቋም አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት፣ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በየጊዜው ማስታወስ፣ ማረጋገጥና መከታተል ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የስራ አንድ አካል አድርጎ መተግበርና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ስለ አካል ጉዳተኞች ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ሰነድ በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፍቅሬ ሙሉጌታ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የእኩል እድል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በዘርፉ በተለይ ቀጥተኛ ሚና ያላቸውን አካላት ማስገንዘብና አስፈላጊውን ኃላፊነት አንዲወጡ ማስቻል፣ በውጤቱም መብቶቻቸው ተከብረው ተሳትፎአቸው እንዲያድግ ተገቢው ማሻሻያ እንዲደረግ እና ወደ ትግበራ መግባት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
እንደ ተቋም የስራ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራና፤ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው የገለፁት ወ/ሮ ፍቅሬ፡፡
የፓናል ውይይቱን የመሩት የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዲ/ን ተስፋው ባታብል ሲሆኑ ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎችና ለተሰጡ አስተያዬቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተቋሙ በሚያከናውናቸው ተግባራትና የምላሽ ስራዎች፣ በሚያወጣቸው የተለያዩ ፖሊሲዎችና የአሰራር መመሪያዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ተግባር የሚያከናውን እንዲሆን መግባባት ላይ ተደርሷል።
“አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት – ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት!”
