በቡግና ወረዳ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች የሰበዓዊ ድጋፍ እየገባ ነው፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀንን አክብሯል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን በዋናነት የግንዛቤ መፍጠሪያ ነው ብለዋል፡፡
በቅድመ አደጋ እና በአደጋ ጊዜ የሚሠሩ ሥራዎችን ለመለየት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አደጋ ከመከሰቱ በፊት የቅድመ መከላከል እና በአደጋ ጊዜ ደግሞ ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡
በችግር ጊዜ ድጋፍ ከማቅረብ ባለፈ ማኅበረሰቡ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ዜጎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የአደጋ ስጋት ቅነሳን በጋራ መሥራት ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ ሲፈለግ የሚሠራ ሳይፈለግ የማይሠራ አለመኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ ከ700 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደሚኖሩ ነው የገለጹት፡፡
ለተፈናቃይ ወገኖች ምላሽ እየተሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል። ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ የሚያደርጉባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ላይ ለገጠመው ችግር ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሰበዓዊ ድጋፍ መግባቱን ተናግረዋል፡ ሰበዓዊ ድጋፉ ቀጣይነት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ የደረሰውን ጉዳት የሚለይ አጥኝ ቡድን ገብቶ እያጠና መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ከምግብ አቅርቦት ችግሩ ጋር ተያይዞ የጤና ችግር እንዳይኖርም ጥናት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የሰበዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተቀናጀ ድጋፍ እየተሰጠ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
ምን ያክል ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በጥናት እንደሚለይም ገልጸዋል፡፡ የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለቅጽበታዊ አደጋ ምላሽ የሚኾን መጠባበቂያ አቅርቦት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ እና ዞን በምግብ ራስን ለመቻል ብሎም የአደጋ ምላሽ ለመስጠት ማልማት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡
ከጥገኝነት ራስን ማላቀቅ እና ራስን ለመቻል መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የመረዳት ሥነ ልቡናን ማስተካከል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ለአደጋ ምላሽ ለመስጠት ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ድርጅቶች እርዳታ ብቻ ከሚሰጡ ልማት ላይ እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ከድህነት የሚያወጣው ልማትን ማረጋገጥ ሲቻል መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

All reactions:
1313
