አይችሉም ሲሉን ችለን አሳይተን፣ ታሪክ ሰርተናልና በህዳሴ ግድብ ልንኮራ ይገባል:ዲ/ን ተስፋው ባታብል (ኮሚሽነር)

የአብክመ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አመራሮች እና ሰራተኞች የሕዳሴ ግድብ ምረቃ በዓልን አስመልክቶ ” በህብረት ችለናል ” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት አድርገዋል።

የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአብክመ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዲ/ን ተስፋው ባታብል ሲሆኑ የሕዳሴው ግድብ መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተሳስረውና ተባብረው የገነቡት፤ የዘመናትና የጋራ ቁጭት የነበረ፣ በራስ ገንዘብ፣ እውቀትና ጥበብ ወደ ድል የተቀየረበት ዳግማዊ አድዋ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ባለድል እንደምንሆን የትናንቱ የአባቶቻችን ታሪክ ምስክር ነው። ዛሬም ታሪክ ሰርተናል ሲሉ ተደምጠዋል። የዚህ ዘመን ዜጎች የሕዳሴ ግድብ የታሪክ ባለቤት በመሆናችን ልንኮራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። አይችሉም ያሉንን ችለን አሳይተን በዓለም አደባባይ ልንኮራ ችለናል ብለዋል።

የሕዳሴው ግድብ እውን መሆን ለኢትዮጵያውያን ያለውን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ ፋይዳ የሚዳስስ የውይይት መነሻ ጽሁፉ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ወ/ሮ ሰርክአዲስ አታሌ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ዉይይት ተደርጓል።

የውይይት መነሻ ጽሑፉ ከቀረበ በሗላ ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሱ ውይይት ተደርጓል። ውይይቱን የመሩት ዲ/ን ተስፋው ባታብል (ኮሚሽነር)፣ ወ/ሮ እታገኘሁ አደመ (ምክትል ኮሚሽነር) እና ወ/ሮ ሰርክአዲስ አታሌ ናቸው።

በሕዳሴ ግድቡ ዘር፣ ማንነት፣ ኃይማኖት፣ ፓለቲካ፣ የእድሜ ደረጃና ጾታ ሳይለየን እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር በአንድነት ቁመን ታሪክ ቀይረናል፣ የቀደመ የአሸናፊነት ልዕልናችን ዳግም አድሰናል፣ ዓለምንም አስደምምናል።

የሕዳሴው ግድብ ትልቅ ታሪክ የተመዘገበበት፣ ታላቅና የገዘፈ ድል እንደሆነ ተገልጿል። በዚህ ግድብ ጅማሮና የግንባታ ሂደት ያለፉ ሁሉ የድሉና የፍጻሜው ባለታሪኮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የነበረውን ውስብስብ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ በማለፍና ጫናውን በመቋቋም እንደ ሀገር በራስ አቅም የተገነባ የአሸናፊነትና የድል አክሊል ነው።

በአባይ ጉዳይ ሁሉም አካል የሀገር አምባሳደር መሆን እንደሚገባው ሌላው የተነሳ ሀሳብ ነው።

ሕዳሴ የዳግማዊ ድላችን ብስራት፣ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ‼️

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top