
በዝናብ እጥረት ለችግር ለተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ ።

መማር አለባቸው፣ ኢብራሒም ዳውድ/ሙባረክ ዘሐበሻ እና ሰሎሜ ጠለምት ወረዳ በዝናብ እጥረት ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ2 መቶ በላይ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አድርገዋል።
በመማር አለባቸው የቲክቶክ ገጽ ከሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ በሚገኙ ቅን ልቦች በተሰበሰበ ገንዘብ 2 መቶ 10 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል። የተደረገው የድጋፍ እህል ከ 1 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ እንደተገዛ የሃገር ውስጥ አስተባባሪው አቶ ኢብራሒም ዳውድ /ሙባረክ ዘሐበሻ ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሠላምይሁን ሙላት ለተደረገው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል። በዞኑ ባሉ ሁለት ወረዳዎች ማለትም በጠለምት ወረዳ እና በምስራቅ ጠለምት የዝናብ እጥረት መከሰቱን እና ነዋሪዎች ለችግር መጋለጣቸውን ኃላፊው አውስተዋል። ለእነዚህ የተቸገሩ ማህበረሰቦችም በሠላም ወልቃይት እና ጓደኞቿ የተሰበሰበ 3 ነጥብ አንድ ሚሊየን ብር የተገዛ 670 ኩንታል እህል መርዳታቸውን ተናግረዋል። ይህን ድጋፍ ኢብራሒም ዳውድ እና ጓደኞቹ ከሁለት ሣምንት በፊት ለ4 ሺ 4 መቶ 67 ተጎጂዎች የሚሆን ከቦታው በአካል በመገኘት ማሰራጨታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም እነዚህ አስተባባሪዎች በድጋሚ 210 ኩንታል እህል ቦታው ድረስ በመገኘት ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ሠላምይሁን ተናግረዋል። ድጋፉ የ1 ሚሊየን አንድ መቶ ሺ ብር መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ድጋፍ ላደረጉ ላሰባሰቡትና በሃገር ውስጥ በማስተባበር ቦታው ድረስ በመሄድ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ሁሉ በዞኑ ማህበረሰብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም ሌሎች ቅን ልቦች በመተባበር ለችግር የተጋለጡ ማህበረሰቦችን እንዲረዱ አሳስበዋል።
ሰው ተኮር ተግባር
