የወረዳ አደጋ ስጋት ቅነሳ ዕቅድ ትግበራ ተግባርን ተቋማት የስራቸው አንድ አካል ሊያደርጉት ይገባል: ም/ል ኮሚሽነር ሰርካዲስ አታሌ

የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በአዉሮፓ ህብረት ገንዘብ ድጋፍ ያልተማከለ አደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ አመራርን ማጠናከር ፕሮጀክት አማካኝነት ለምስራቅ አማራ 5 ዞኖች የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ተ/ጽ/ቤት የቅ/ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪዎች እና ባለሙያዎች እና ከ 5ቱ ዞኖች ከመጡ 13 ወረዳዎች የቅ/ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪዎች ጋር በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ እና አካቶ ትግበራ (DRM policy and mainstreaming) ላይ ከጥቅምት 11/2018 ዓ.ም ጀምሮ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በስልጠናዉ ላይ ተገኝተዉ ስልጠናዉን በይፋ ያስጀመሩት የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ ሰርካዲስ አታሌ ኮሚሽኑ እንደገለጹት ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጋር በትብብር እስካሁን የበርካታ ወረዳዎችን የአደጋ ተጋላጭነት ፕሮፋይል ጥናትና ዕቅድ ዝግጅት ሲተገብር የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ የተዘጋጁ የወረዳ አደጋ ስጋት ተጋላጭነት ፕሮፋይል እና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዕቅዶችን መረጃ በመጠቀም የአደጋ ስጋትን ሊቀንስ የሚችል የወረዳ አደጋ ስጋት ቅነሳ ዕቅድ ትግበራ ስራዉን በየሴክተር መስሪያ ቤቱ ዓመታዊ ዕቅድ ዉስጥ አካቶ በመተግበር ዙሪያ ዉስንነቶች የነበሩበት መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ስራ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያዉ ክፍል በክልሉ ከ15 ያልበለጡ ወረዳዎች ላይ በጅማሮ የሚገኝ ቢሆንም በዚህ ዓመት በፕሮጀክቱ 6 እና በመደበኛዉ 16 ወረዳዎች በድምሩ 22 ወረዳዎች እቅድ በመያዝ ኮሚሽኑ በልዩ ትኩረት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለመተግበር በእቅድ የተያዘ መሆኑን ገልጸዉ የስልጠናዉ ተሳታፊዎች ይህን ዕቅድ ለማሳካት ከስልጠናዉ በቂ ግብዓቶችን መዉሰድ እንደሚገባቸዉ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

ስልጠናዉ በ2016 የተከለሰዉ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ፣ በሁሉን አቀፍ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ዕቅድ አስተቃቀድ እና አካቶ ትግበራ ርዕሶች ላይ አተኩሮ እንደሚሰጥ ገልጸው ሰልጣኞች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰለጥኑና በስራ ላይ እንዲያውሉት አሳስበዋል።

ከስልጠናዉ በተጨማሪም ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሰርካዲስ አታሌ የፕሮጀክት የትግበራ ወረዳዎች ቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪዎችን በመያዝ በአደጋ ስጋት ዕቅድ ትግበራ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ ዕቅዱን ለመፈጸም አሁን ላይ በየወረዳቸዉ ከቅድመ ዝግጅት ስራ ጀምሮ እስከ ትግበራ ትኩረት ሊሰጥባቸዉ ስለሚገባ ጉዳዮች ሰፊ ዉይይት አድርገዋል።

የፕሮጀክቱ ወረዳዎች ቡድን መሪዎችም ይህን እቅድ ለማስፈጸምና ለመፈጸም ከራሳቸዉ ጀምሮ በወረዳዎች ላይ ያለዉን ቁርጠኝነት እንዲሁም ሊያጋጥሟቸዉ ስለሚችሉ ችግሮች አንስተዉ ምክክር የተደረገ ሲሆን ተግባሩን በልዩ ትኩረት በመያዝ መነሻ ጥናት እስከ ቀጣይ 10 ቀን አጠናቀው እንዲልኩ ምክትል ኮሚሽነር ሰርካዲስ ጥብቅ አቅጣጫ በመስጠት አጠናቀዋል::

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top