“ኮሚሽኑ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራርን በማጠናከር ለአደጋ የማይበገር ማህበረሰብ ለመፍጠር ተግቶ እየሰራ እንደሆነ ተገለጸ”

የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከኮሚሽኑ ሰራተኞች ጋር በዛሬው ዕለት ማለትም በ18/02/2018 ዓ/ም የግምገማ መድረክ አካሂዷል።

የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ወ/ሮ ሠርካዲስ አታሌ ሲሆኑ የመድረኩ ዓላማ በ1ኛው ሩብ ዓመት በጥንካሬ የተፈጸሙትን ለማስቀጠል፣ በነበሩ ድክመቶች ዙሪያ ለመነጋገር ብሎም ለማሻሻልና በቀጣይ ውጤት ለማስመዝገብ ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛውን ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን የሚያሳይ ሪፖርት በኮሚሽኑ የዕቅድና በጀት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ማናዬ አማርኸኝ ቀርቧል። በሪፖርቱም የ2018 በጀት ዓመት ግቦችና ዋና ዋና ተግባራት፣ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም፣ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ስራዎች፣ የአበይት ተግባራት አፈጻጸም፣ የሀብት አጠቃቀም፣ በአፈጻጸም ሂዳት ያጋጠሙ ችግሮች እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተካተው በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በግምገማዊ መድረኩ ተሳታፊ ሰራተኞች ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን የመሩት ምክትል ኮሚሽነር ሠርካዲስ አታሌ እና የኮሚሽኑ አማካሪ የሆኑት አቶ አንሙት በለጠ ሲሆኑ ለተነሱ ጥያቄዎችና ለተሰጡ አስተያዬቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጧል።

የአደጋ ሥጋት ስራ አመራርን በማጠናከር የክልሉን ህዝብ የአደጋ መከላከልና መቋቋም አቅም ማጎልበት ተገቢ ነው ተብሏል። የመጠባበቂያ ክምችትን ለማሳደግና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ሁሉም በየደረጃው ያለ አካል ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተነስቷል በመድረኩ።

የምግብ ክፍተትን በመሙላት፣ ስርዓተ-ምግብንና የኑሮ መሰረቶችን በማሻሻልና ከተረጅነት ለመውጣት ተግቶ መስራት ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር እንደሆነ በመድረኩ ሌላው የተነሳው ሀሳብ ነው።

የላቀ የቅድመ አደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ውጤታማ የአደጋ ዝግጁነትና ቀልጣፋ ምላሽ፣ ድህረ አደጋ ልማትና የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ ሀብት ማሰባሰብና ስትራቴጂያዊ አጋርነትን ማጠናከር የኮሚሽኑ ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮች እንደሆኑ ተገልጿል።

በመጨረሻም ወ/ሮ ሠርካዲስ አታሌ (ምክትል ኮሚሽነር) የክልሉን የምላሽ አቅም በየደረጃው ማጠናከር፤ የእለት ምግብ ድጋፍ በወቅቱ ማሰራጨት፣ ተፈናቃዮችን መደገፍና በቀጣይ እንዲመለሱ በትብብር መስራትና መልሶ ማቋቋም፣ በየደረጃዉ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት ይዞ መምራትና መከታተል፣ የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነትን ማሻሻል፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመርና ተደራሽ ማድረግ፤ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፣ ለዞንና ለወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ስራን በቅንጅት መምራት በቀጣይ ትኩረት ተሰጧቸው የሚሰሩ ተግባራት እንደሆኑ አቅጣጫ አስቀምጠው ውይይቱ ተጠናቋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top