የመጠባበቂያ ሀብት አሰባሰብን በማጠናከር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅምን ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:ም/ል ኮሚሽነር ሠርካዲስ አታሌ

የአብክመ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የ2ዐ18 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም በምዕራብ አማራ ከሚገኙ የዞን ተጠሪ ጽ/ቤቶች ጋር ግምግማ አካሂዷል፡፡

የግምገማ መድረኩን አስመልክቶ ለተሳታፊዎች የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሠርካዲስ አታሌ እንደገለጹት የ2ዐ18 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸማችንን በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎችን አጎልብተን ለማስቀጠል እና ክፍተቶቻችንን አርመን በ2ኛው ሩብ አመት አጠናክረን ለመስራት የሚያስችል የግምገማ ግብአት የምናገኝበትና አፈጻጸማችን በውጤት የምናጀብበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

የበጀት አመቱ የ1ኛው ሩብ ዓመት የተጠቃለለ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በኮሚሽኑ የዕቅድና በጀት ዝግጅት ግምገማና ክትትል ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ማናየ አማርኸኝ ቀርቧል፡፡ በሪፖርቱም በተቋም አቅም ግንባታ፣ በአበይት ተግባራት በቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ፣ በህዝብ ግንኙነት፣ በዕቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ፣ በምግብ ራስን መቻል ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በዝርዝር ለመድረኩ ተሳታፊዎች ቀርበዋል። በተጨማሪም የዞን ተጠሪ ጽ/ቤቶች አፈጻጸም ደረጃ ቀርቦ ተገምግሟል።

በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን የመሩት ወ/ሮ ሰርካአዲስ አታሌ (ምክትል ኮሚሽነር) እና አቶ አንሙት በለጠ (የኮሚሽኑ አማካሪ ) ሲሆኑ በአፈጻጸሙ ሪፖርቱና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎችና ለተሰጡ አስተያዬቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ቅነሳ ተግባራትን በማከናወንና የመጠባበቂያ ሀብት አሰባሰብን በማጠናከር የዝግጁነት አቅምን ማሳደግ ከወትሮው በተለዬ ሁኔታና ቁርጠኝነት ትኩረት ተሰጦት ሊሰራ ይገባል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነር ሠርካዲስ

በምግብ ራስን መቻልና ከተረጅነት መውጣት የሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ በመሆኑ ዞኖች ታች ቀበሌ ድረስ በተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ከሌሎች የሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል የምናደርገው ጥረት የምግብ ክፍተትን በመሙላት ከተረጅነት ለመውጣትና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከላይ እስከ ታች ያለ አመራር፣ ባለሙያ እና ማህበረሰቡ በቁርጠኝነት ጉዳዩን ይዞ እንዲሰራ እንደ አስተባባሪ ተቋም የሃብት አሰባሰባችንን በየአካባቢው አጠናክሮ መስራት እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

ኮሚሽኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የዕለት ምግብ ድጋፍ በማቅረብ ህይዎት እየታደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ምክትል ወ/ሮ ሠርካአዲስ አታሌ (ምክትል ኮሚሽነር) በ2ኛው ሩብ አመት በልዩ ትኩረት ሊከናውኑ ይገባል በተባሉት ተግባራት ዙሪያ አቅጣጫ ሰጥተዉ የአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top