በዓለማቀፍ ደረጃ ለ35ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ “ለአረጋዊያን ደህንነት እና መብቶች መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ-ቃል የተከበረውን የአረጋውያን ቀንን ምክንያት በማድረግ የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አመራርና ሰራተኞች የፓናል ውይይት አካሂደዋል።





የአብክመ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዲ/ን ተስፋው ባታብል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአረጋዊያንን ደህንነት መጠበቅ፣ መንከባከብና ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ሰብዓዊ ግዴታን መወጣት መሆኑን ገልጸው ሀገርን በክብር ያቆዩ አረጋዊያንን መንከባከብ፣ እውቀትና ልምዳቸውን መጠቀም የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑም ተናግረዋል፡፡
የአረጋውያንን ቀን ለማክበር የተዘጋጀ የውይይት መነሻ ሰነድ በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፍቅሬ ሙሉጌታ አቅርበዋል። በሰነዱም የአረጋዊያንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በአካቶ ትግበራ ስራ መስራት ተገቢ እንደሆነ፣ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ መዘከር፣ እዉቅና መስጠት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸዉን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በቀረበው ሰነድ ዙሪያ ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሱ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱም የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋዊያንን በሁሉም መስክ ማሳተፍ እና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ፣ ባለደርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው፣ አረጋዊያንን መንከባከብ እና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት እንደሆነ ተነስቷል።
ውይይቱን የመሩት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር የሆኑት ዲ/ን ተስፋው ባታብል ለተነሱ ጥያቄዎችና በተሰጡ ሀሳቦች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“ለአረጋዊያን ደህንነት እና መብቶች መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ”
26/03/2018 ዓ/ም
