“የፕሮግራሙ የመጨረሻ ግብ ተጠቃሚዎችን ራሳቸውን አስችሎ ማስመረቅ ነው” ዲ/ን ተስፋው ባታብል (ኮሚሽነር)

የአብክመ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ከግብርና ቢሮ፣ ከገንዘብ ቢሮ እና ከሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በቅንጅት በምዕራብ አማራ የሚገኙ ተጠሪ ጽ/ቤቶች፣ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የሴፍቲኔት ፕሮግራም ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በ02/12/2017 ዓ/ም በባህርዳር ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአብክመ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲ/ን ተስፋው ባታብል የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የመጨረሻ ግብ ተጠቃሚዎችን ራሳቸውን አስችሎ ማስመረቅ ነው ብለዋል። ተጠቃሚዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ ከተረጅነት አስተሳሰብ በመውጣት ራሳቸውን እንዲችሉና በዘላቂነት እንዲቀቋሙ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዲያቆን ተስፋው ባታብል (ኮሚሽነር) ባሳለፍነው በጀት ዓመት በችግር ውስጥ ሆኖ ፕሮግራሙ በርካታ ተግባራትን በማከናወን አመርቂ ውጤት እዳስመዘገበ ገልጸው፣ ተጠቃሚ የሆኑ የፕሮግራሙ ደንበኞችን ህይወት የሚቀይርና ከድህነት የሚያወጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እደተከናወኑ አስረድተዋል።

የሴፍቲኔት ፕሮግራም የተሟላ ሀብት ያለው፣ አበርክቶውም የጎላና የሚታይ እንዲሁም የሚለካ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም ከምንጊዜውም የተሻለ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከወረዳ እስከ ክልል ያለው ስትሪንግ ኮሚቴ ተግባራቱን እየገመገመ በመምራቱና በቅንጅት በመስራቱ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል።

የከፋ ድህነትን በመቀነስ ለአደጋ የማይበገርና በዘላቂነት የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም አካል ሊረባረብ ይገባል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top